መግቢያ

ይህ ረቂቅ ሰነድ ኢትዮጵያውያን ከትግሬዎች እና ኤርትራውያን ጋር በአንድ ሀገር በሰላም መኖር ስላልቻሉ እና ከፍተኛ የሆነ ዕልቂት እና ሰቆቃ ስለደረሰ አሁን ያለው አማራጭ ተለያይቶ በጉርብትና መኖር ነው ብሎ ያምናል።ኤርትራውያን 30 ዓመት በላይ ትግሬዎች ደግሞ ከ 17 ዓመት በላይ ከቀሪው የ ኢትዮጵያ ክፍል ተገንጥለው የራሳቸውን ሀገር ለመመስረት ታግለዋል። በዚህም መሰረት ኤርትራውያን የራሳቸውን ሀገር ሲመሰርቱ ትግሬዎች ግን የመገንጠል ሃሳባቸውን ለግዜው አዘግይተው በመላው የ ኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ በተለይም በ አማራ እና ኦሮሞ ሕዝብ ላይ ከፍተኛ ሰቆቃ እና በደል እያደረሱ ይገኛሉ። ይህን ተከትሎ ከፍተኛ የሆነ ሕዝባዊ ቁጣ እና አመፅ ከዳር ዳር ተቀጣጥሉዋል። የኦሮሞ ወይም አማራ ሀገር ምስረታ ከሚሊዮኖች በላይ የሰው ሕይወት የሚቀጥፍ ደም መፋሰስ ያስከትላል። ኦሮሞ እና አማራ በከፍተኛ ሁኔታ ተቀላቅለው ስለሚኖሩ እና አሰፋፈራቸው የተቀላቀለ ስለሆነ የየራሳቸውን ሀገር ሊገነቡ አይችሉም። ሸዋ አዲስ አበባን ጨምሮ ፣ወሎ/ላኮመልዛ፣ ሐረርጌ፣ ጅማ/ከፋ፣ ወለጋ፣ ጎጃም እና ሌሎች ቦታዎችን ብናይ ነገሩ ምን ያህል ውስብስብ እንደሆነ እንረዳለን። በዚህ ሰነድ የሀገሪቱ አስተዳደር መልክዐምድርን እና የህዝቦች አሰፋፈር መሰረት ያደረገ ያልተማከለ (የፌዴራል ) ስርአት ይሆናል። አማርኛ እና ኦሮምኛ የሀገሪቱ የስራ ቋንቋዎች ይሆናሉ። አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ቀለማት እና ከላዩ ላይ የኦዳ ዛፍ ያለበት ሰንደቅ አላማ የሀገሪቱ ሰንደቅዓላማ ይሆናል። መፍትሄው አማኦሮ/ኦሮማራ ነው። የሀገሪቱን 80% በላይ የሚሸፍኑት እነዚህ ሁለት ህዝቦች ከቀሪዎቹ ኢትዮጵያውያን ጋር በጋራ ሁነው ለሁሉም የሚሆን ስርዓተ ማህበር መገንባት ይችላሉ። ለዚህም ሂደት ይረዳ ዘንድ ይህን የሽግግር ግዜ ረቂቅ ሰነድ አዘጋጅቼ አቅርቢያለሁ። በዚህ የሽግግር ሰነድ መሰረት ትግሬዎች ከ1983 ዓ.ም በፊት በነበረው የግዛቶች አከላለል መሰረት ያላቸውን መሬት ይዘው የራሳቸውን የትግራይ መንግስት መስርተውም ይሁን ከኤርትራውያን ጋር በመቀላቀል ከኢትዮጵያውያን ጋር በመልካም ጉርብትና መኖር ይችላሉ። ይህን አሻፈረኝ ብለው ኢትዮጵያውያንን እየጨቆኑ እና የነሱ ያልሆነ መሬት ላይ ተስፋፍተው ለመኖር ከወሰኑ ግን ለእነሱም ለማንም አይበጅም። የአሰብ ወደብ የኢትዮጵያ ባለቤትነት በዚህ ረቂቅ ሰነድ ላይ ተካቷል። ይህ ወደፊት ከኤርትራውያን ጋር ዘላቂ ሰላም እና መልካም ጉርብትና የሚያመጣ ነው።

ይህ የሽግግር ግዜ ሰነድ እንደመነሻ የቀረበ ሲሆን የተለያዩ ድርጅቶች ለሚያዘጋጁት ሰነድ ግብአት ይሆናል የሚል እምነት አለኝ። ሊስተካከሉ ፣ሊጨመሩ እና ሊካተቱ የሚችሉ ሌሎች ሃሳቦች ይኖራሉ። በሁሉም ድርጅቶች እና የህዝብ ወኪሎች ውይይት ተደርጎበት ተቀባይነት ካገኝ ይህ ረቂቅ ሰነድ ለሶስት አመታት የሀገሪቱ የበላይ ሕግ ሁኖ ይሰራል። የሶስት ዓመት የሽግግር ግዜ ይኖራል።

የሀገሪቱ ስያሜ
”ህዝባዊት ኢትዮጵያ” ይባላል

የሽግግር መንግስቱ ስያሜ
”የሕዝባዊት ኢትዮጵያ የሽግግር መንግስት” ይባላል

ኢትዮጵያዊ ዜግነት
በ ኢትዮጵያ ውስጥ የተወለዱ ወይም በየትኛውም የዓለም ክፍል ተወልደው ቢያንስ አንድ ቤተሰባቸው ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ ኢትዮጵያዊ ናቸው።

የሀገር እና የስልጣን ባለቤትነት
ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ የሀገሩ ባለቤት ነው። መላው የ ኢትዮጵያ ሕዝብ የስልጣን ባለቤት ነው። የ ስልጣን ሁሉ ምንጭ የ ኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። ኢትዮጵያ የተለያዩ ነገዶች ፣ ቋንቋዎች፣ እምነቶች እና ባህሎች ያሉባት ሀገር መሆኗን እውቅና ይሰጣል።

የ ኢትዮጵያ የሽግግር መንግስት የአስተዳደር አይነት፣ ግዛቶች እና ስያሜዎች
የሽግግር መንግስቱ መልካዓምድርን እና የህዝቦችን አሰፋፈር መሰረት ያደረገ ያልተማከለ (የፌደራል) ስርዓት ይኖረዋል። የሽግግር መንግስቱ የማዕከላዊው መንግስት እና የአስተዳደር ግዛቶቹ ስልጣን እና ግንኙነት በሽግግር መንግስቱ ምክር ቤት የሚወሰን ይሆናል። የሽግግር መንግስቱ 12 የአስተዳደር ግዛቶች ይኖሩታል። አከላለሉ እና ስያሜው ከ1983 ዓ.ም በፊት በነበረው መሰረት ይሆናል። ረቂቅ የአስተዳደር ካርታው ከዚህ ፅሁፍ ጋር ተያይዟል።ስያሚያቸውም በጌምድር፣ ጎጃም፣ ወሎ፣ ሸዋ፣ ወለጋ፣አርሲ ፣ሐረርጌ ፣ባሌ፣ ሲዳሞ፣ ጋሙ ጎፋ፣ ከፋ እና ኢሉባቡር ይሆናሉ።

የሽግግር መንግሥቱ የስራ ቋንቋ
በአብዛኛው ህዝብ የሚነገሩት አማርኛ እና ኦሮምኛ የሽግግር መንግሥቱ የስራ ቋንቋ ይሆናሉ። በሂደት የሀገሪቱ አቅም ሲፈቅድ አንድ መቶ ሺህ እና ከዛ በላይ ተናጋሪ ያላቸው ቋንቋዎች የመንግስት የስራ ቋንቋዎች ይሆናሉ። በየአስተዳደር ግዛቶቹ ከማዕከላዊው የሽግግር መንግስት የስራ ቋንቋዎች በተጨማሪ በየግዛቶቹ የሚነገሩ ሌሎች ቋንቋዎች ለየ አስተዳደር ግዛቶቹ በሥራ ቋንቋነት ያገለግላሉ።

የባህር በር ባለቤትነት
የአሰብ ወደብ በወሎ ግዛት ስር ሁኖ የኢትዮጵያ የባህር በር ይሆናል።
የሀገሪቱ ሰንደቅ አላማ
አረንጉዋዴ ቢጫ እና ቀይ ቀለማት ላይ የኦዳ ዛፍ ምልክት ያለበት ሰንደቅ አላማ የሽግግር መንግስቱ ሰንደቅ አላማ ይሆናል።አረንጉዋዴ ቢጫ እና ቀይ ቀለማት የ አማራን ሕዝብ ታሪክ እና ማንነት የሚገልፅ ሲሆን የዛፍ ወይም የኦዳ ምልክት ደግሞ የ ኦሮሞን ሕዝብ ታሪክ እና ማንነት የሚገልፅ ነው። የ ኢትዮጵያ 75-80% የሚሆነው ሕዝብ የነዚህ ሁለት ሕዝቦች ድምር ውጤት ነው። በዘላቂነት ለሀገሪቱ የሚሆነው ሰንደቅ አላማ ወደፊት በሚዘጋጀው ህገ መንግስት ላይ ተካቶ ህዝበ ውሳኔ ይደረግበታል።

የሽግግር መንግስቱ ዋና ከተሞች
የሽግግር መንግስቱ ስድስት ዋና ከተሞች ይኖሩታል። እነሱም አዲስ አበባ፣ ባህር ዳር፣ አምቦ፣ ጎንደር ፣ሀዋሳ እና ድሬዳዋ ይሆናሉ ።

የሽግግር መንግስቱ ምክር ቤት አወቃቀር እና የህዝብ አወካከል
ሁሉም የፖለቲካ፣ የማህበራዊ፣ ሃይማኖታዊ እና የ ሲቪክ ድርጅቶች እና ማህበራት የሚሳተፉበት የሽግግር መንግስቱ ምክር ቤት ይቋቋማል።የሽግግር መንግስቱ ምክር ቤት አወካከሉ የ ነገድ ስብጥርን ያማከለ ይሆናል ። በገለልተኛ ወገን አዲስ የህዝብ ቆጠራ እስኪካሄድ ድረስ ከ1983 ዓ.ም በፊት በተደረገው የህዝብ ቆጠራ ስሌት መሰረት እያንዳንዱ ነገድ እንደህዝብ ብዛቱ መጠን በነገዱ ስም በተደራጁ ድርጅቶች አማካኘነት በሽግግር መንግስቱ ምክር ቤት ይወከላል። የ ኢትዮጵያ ሕዝብ በነገድ ማንነቱ ሳቢያ ብዙ በደል ስለደረሰበት ሙሉ መብቱ እና ማንነቱን ለማረጋገጥ የነገዶች ስብጥርን መሰረት ያደረገ ውክልና በሽግግር መንግስቱ ውስጥ አስፈላጊ ነው። በዘላቂነት በሚረቀቀው ህገ መንግስት ላይ ግን ይህ የ እያንዳንዱ ነገድ ሙሉ መብት ከተከበረ እና መተማመን ላይ ከተደረሰ በሁዋላ የህዝቡ ፍቃድ ከሆነ ዜግነትን መሰረት ያደረገ የህዝብ አወካከል ሊኖር ይችላል ። የሽግግር መንግስቱ ምክርቤት የሽግግር ግዜ መንግስት ያቋቁማል። የሽግግር ግዜ ምክርቤቱ ሕግ እና ደንብ ያወጣል። ሥራ አስፈፃሚ የሚሆን የሽግግር ወቅት የሚንስትሮች ምክርቤት ያዋቅራል። የሚንስትሮች ምክርቤትን የስራ ድርሻ እና ኃላፊነት በዝርዝር ያወጣል። ነፃ እና ገለልተኛ ዳኞችን በመሾም ነፃ እና ገለልተኛ የሆነ የሽግግር ጊዜ የፍትህ አካል ያቋቁማል። የሕገ መንግስት አርቃቂ ቡድን አዋቅሮ በሁለት ዓመት ግዜ ውስጥ ለሕዝበ ውሳኔ የሚቀርብ ህገ መንግስት/ህገመንግስቶች ያዘጋጃል። የሽግግር መንግስቱ ግዛቶችን ስልጣን፣ የስራ ድርሻ ፣ ኃላፊነት እና ከ ማዕከላዊው አስተዳደር ጋር የሚኖራቸውን ግንኙነት ይወስናል።

Share.

About Author

Comments are closed.