ከህወሓት/ኢህአዴግ ካምፕ ወደ ሀብታሙ አያሌው በኢንጂነር ግዛቸው የተተኮሰች ቀስት።

0

ከህወሓት/ኢህአዴግ ካምፕ ወደ ሀብታሙ አያሌው በኢንጂነር ግዛቸው የተተኮሰች ቀስት።
======================
ለግዛቸው ሽፈራው (ኢንጂነር)
በቅድሚያ ከላይ በሰጠሁት ርዕስ ቅር የማሰኘው አካል ቢኖር ይቅርታዬን እሰዳለሁ። ለዝች አጭር ፅሁፍ መነሻ የሆነኝ ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው በሳተናው ድረ ገፅ ላይ ያወጣው ፍሬ ከርስኪ ፅሁፍ ነው የፅሁፉ ይዘትም የማውቃትን ትንሽ ነገር ለማለት ያህል እንጂ ለሀብታሙ አያሌው ጥብቅና ለመቆም አለመሆኑም ይታወቅ። ፀሀፊው በጀመረው የስም ማጥፋት ዘመቻ ላይ ያድበሰበሳቸው ከእውነት ያፈነገጡ አረፍተ ነገሮች ችላ የማይባሉ ህወሀት/ ኢህአዴግ ስለምን ገበናው ተገለጠብኝ ብሎ የሚሟገት የወያኔ ጠበቃ ያስመስለዋል። ኢንጂነሩ እራሱ ወያኔን በኮሚሽነርነት ሲያገለግል የነበረና በኤርትራ ትገንጠል ጥንስስ ጊዜ በርካታ ምሁራን ሀገር ትፈርሳለች እያሉ ድምፃቸውን ከፍ አድርጎ በሚጮሁበት ጊዜ ከነ አፄ መለስ ጋር አብሮ ሀሳባቸውን በመደገፍ ማስገንጠሉ እየታወቀ ሌላውን ኢህአዴግ ነበርክ ለማለት ሞራል ማግኘቱ አንዴ በስብሻለሁና ዝናብ አልፈራም ከማለት ውጭ ይህን የሞራል ክስረት ከየት አመጣው ?ሀብታሙስ ወደ አንድነት ፓርቲ ሲመጣ የቀድሞው አንድነት ፓርቲ በስራ አስፈፃሚ አፅድቆት ምክር ቤቱ ተነጋግሮበት እንጂ በግለሰቡ ፍላጎት አለመምጣቱን እንዴት ዘነጋው?የሳተናው ዌብ ሳይት ባለቤትስ ማን ነው ? ለምንስ በተደጋጋሚ በወጣቱ ፖለቲከኛ እና በቀድሞው አንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ በሀብታሙ አያሌው ላይ ከፍተኛ የሆነ የስም ማጥፋት ዘመቻ ይከፍታል? አንድነት ፓርቲ የፈረሰው ሀብታሙ በግዛቸው ጥቆማ እና በህወሀታውያን አስፈፃሚነት ከታሰረ ከ 8 ወራት በኋላ መሆኑ እየታወቀ የስም ማጥፋት ዘመቻው እና አንባቢን ለማጭበርበር መሞከሩ ምን አይነት ድንክ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ታስቦ ነው? ሀብታሙ ከታሰረ በኋላ ፀሀፊው ግዛቸው ሽፈራው ጀግና አመራራችን ታሰረ እያለ ፍርድቤት እየተመላለሰ በድጋሚ ምርጫ ለማለፍ ሲሞክር እና መግለጫ ሲያወጣ ኑሮ አሁን ከህወሀት ሰማይ ስር በሚለው የሀብታሙ መፅሀፍ ላይ ትችት ሲቀርብበት የስም ማጥፋት ዘመቻውን ለምን መረጠ? የሚሉ ጥያቄዎችን ሊመልሳቸው ግድ ነው። ፀሀፊው በማድበስበስ ያለፋቸው ሌሎች በርካታ ጉዳዮች ቢኖሩም በዋናነት የተወሰኑትን ብቻ አነሳለሁ። ይኸውም የመኢአድ እና አንድነት ፓርቲ ውህደትን በተመለከተ በአንድ ወቅት ወደ ቢሮህ አስጠርተኸኝ ወጣቶቹ ምንድን ነው የምትጠብቁት? የነ ሀብታሙ እና ፀጋዬ አላምረው ግሩፕ የሸዋን ፖለቲካ በጎጃም ፖለቲካ ለመቀየር ጠንክሮ እየሰራ ነው አንድ የሸዋ ሰው እኔ ብገኝ በውህደት ስም ሊያጠፉኝ ነው። በአሁኑ ሰአት በሀገሪቱ ውስጥ ያሉትን የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር ተመልከቱ የኢዴፓው ከበደ ጫኔ፣ የሰማያዊው ይልቃል ጌትነት፣ የመኢአዱ አበባው መሀሪ ከነ 9 ስራ አስፈፃሚ አባላቱ እነዚህ ሁሉ የፓርቲ አመራሮች ጎጃሜ መሆናቸው እየታወቀ ሀብታሙ እና ፀጋዬም በውህደት ሰበብ የጎጃምን የበላይነት ሊያመጡ ነውና ውህደቱ እንዲከሽፍ ጠንካራ የሎቢ ስራ መስራት አለባችሁ ብለህ ለማግባባት ስትሞክር ምን እንደመለስኩልህ የምታውቀው ነው። በቅድመ ውህደት ፊርማው ላይም ፀጋዬ ተነጥሎ በድንጋይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት እንደነበርም የምትክድ አይመስለኝም።
ሌላኛው ግርምትን እና ሳቅን የፈጠረብኝ ነገር በኢንጂነሩ ካቢኔ ውስጥ ያልነበሩትን አቶ አስራት ጣሴን ከሸዋ ወደ አዲስ አበባ ስታመጣቸው ሀብታሙን ከአዲስ አበባ ወደ ወሎ ያሸጋገርክበት መንገድ ሊገባኝ አልቻለም ። ፀሀፊው ስላነሳው ወደ ማልፈልገው የዘር ቆጠራ ብገባም እውነታውን ግልፅ ለማድረግ ያክል ሸዋ ነበሩ ሳይላቸው። የዘለላቸውን ጥቂት አመራሮች እንድጠቅስ ይፈቀድልኝ

የኦዲት እና ኢንስፔክሽን ኃላፊው ሻለቃ አርጋው፣
የፋይናንስ ኃላፊው አቶ አስቻለው ከተማ፣
አፈ ጉባኤው አበበ አካሉ

ዋና ፀሀፊው ስዩም መንገሻ

የእ.አ. ዞን ሊቀመንበር ዘካርያስ የማነብርሃን እራሱ ፀሀፊው እነዚህ ሁሉ ሸዋ መሆናቸውን እያወቀ እና የሸዋ የበላይነት ከሌለ በእግሩ ቆሞ መሄድ አይችልም በማለት ከፍተኛ ውዥንብሩን ሲፈጥር ቆይቶ አሁን በአደገኛ ሙከራው ወሎዬነትን ማሸማቀቂያ ለማድረግ መሞከሩ አሳፋሪም አስነዋሪም ነው። በስተመጨረሻም ሀብታሙ ከመታሰሩ ከሳምንታት በፊት ከአቦይ ስብሀት ጋር በድብቅ እየተገናኘህ ከፍተኛ ድርድር ታደርግ እንደነበረ እና ይህንንም እንደሰማ እና የፓርቲውን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት እና ምክትል ፕሬዝዳንቱን በምስክርነት ጠቅሶ በመፅሀፉ ላይ አስፍሮት ልናነብ ችለናል። የሁለቱ አመራሮች አስተያየትም በመፅሀፉ ውስጥ ሰፍሮ እንደሚገኝ ይታወቃል እና ኢንጅነሩ የተንሸዋረረ አመለካከቱን ትቶ በተጨማሪ የዳንኤል ተፈራን”ሀገር የተቀማ ትውልድ” እና በቅርቡ ያነበብኩትን የግርማ ሰይፉ የተከበሩት የሚሉትን መፅሀፍት እንዲያነብ እመክራለው። ከዚህ በተሻለ ሀብታሙ በስፋት መልስ የሚሰጥባቸው ጉዳዮች እንደሚኖሩ እገምታለሁ። እናም ከከሸፉ አይቀር እንደ ግዛቸው ሽፈራው ስል ፅሁፌን አበቃለሁ።
ዘላለም ደበበ (የእልፌ ልጅ) የቀድሞው አንድነት ፓርቲ መስራች አባልና የህዝብ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ አመራር

ይውደዱተጨማሪ የስሜት መግለጫዎችን አሳይ

አስተያየት

Share.

About Author

Comments are closed.