አሁን ግን ከእንግዲህ ስለኢትዮጵያ ዝም አንልም።

~”~እሳት የለበሰ እሳት የጎርሰ ዝም የማይል ትንታግ ትውልድ መጣላችሁ።

~”~የዘመኑ እግዚአብሔርን የመቃወሚያ ስልቶች እንክትክት ብለው ይሰባበራሉ። አበቃ!!!

ወዳጆቼ አሁን በዚህ ዘመን ሃይማኖታችንን ከሃገራችን፤ ሰውን ከሃይማኖቱ፤ ሥራውንም ከሃይማኖቱ፤ ትምህርት ቤቱም ሃይማኖት አልባ እንዲሆን ተደርጎ የሰው ልጅ መራር በሆነው የዓለማዊነት ክፉ መንፈስ ባሕር እንዲዋኝ ተፈርዶበታል። አውሮፓውያንና ምዕራባዊያን የኢትዮጵያዊያን ንዑድ ክቡር መፅሐፍትና ትሩፋቶች ወስደው እየተመራመሩባቸው ነው። እኛ ደግሞ የራሳችንን ንቀን የእነሱን እንቶ ፈንቶ እየተጋትን ባዶዎች ሆነናል። ባዶ ብቻ። ምዕራባዊያን ይህን እውነት ለማጥፋት ባለፉት ዘመናት በኃይል ሲወርሩንና ሲዘርፉን ከራርመዋል። አሁን ደግሞ ራሱንም፤ ሃይማኖቱንም፤ አገሩንም የማያውቅ ነፈዝ ትውልድ ይፈጠር ዘንድ ሃይማኖት ነው በሚል ሰበብ የምዕራባዊያንን ቅርሻት ወደ አገራችን አስገብተው ሕዝቡን ሲያነሆልሉትና ሲያደነዝዙት ይውላሉ። ይህን የሚተገብሩ ልብ አውልቅ ፓስተርና ነቢይ ነኝ ባይ ሆድ አደር አንጃዎችን አሰማርተዋል። እነዚህ አንጃ ነቢይ ነኝ ባይ ዱርየዎችም አዳራሽ ከፍተው ሕዝብን ሲያታልሉ ከመዋላቸውም በላይ ገንዘብ መሰብሰቢያ ቢዝነስ አድርገውታል። ወዳጆቼ ቅዱሳን ሐዋርያት ይፈውሱ፤ ድውያንን ያድኑ ነበር፣ ሙት ያስነሱ ነበር። ታዲያ ይሄን ሥራቸውን እወቁልኝ አይሉም ነበር። ቅዱሳን የምዕመናን አገልጋዮች እንጂ ተገልጋዮች አይደሉም። ቅድስናቸው ክብራቸውን ይገልጠዋል እንጂ ቅዱስ ነኝና አክብሩኝ ብለው አደባባይ ራሳቸውን ከፍ አያደርጉም። የዛሬዎቹ መናፍስት ጠሪዎች ነቢይነትን በሥልጠና የሚመጣ መስሏቸው የነቢያት ማሠልጠኛ ኮሌጅ እስከ መክፈት ደርሰዋል። ይህንን ድራማቸውንም ዘመን በወለደው ቴሌቪዝን ለሕዝብ ሲግቱት ይውላሉ።

አንድ እዩ ጩፋ የተሰኘ ካራቲስት ከእለታት በአንዱ ቀን ዓይን ጥሎኝ (እግር ጥሎኝ እንዲሉ) በከፈተው ቲቪ ስመለከት የሚሰራውን ድራማ ላጫውታችሁማ። “ሙት ላስነሳ ነው አለ”። ሕዝቡ “አሜን” ይላል።

፡ ካራቲስቱ፦ “ሁለት ሙታንን ላስነሳ ነው።
፡ሕዝቤ፦ “አሜን”
፡ካራቲስቱ፦ “ሁለት ሰዎች ወደ እኔ ሲመጡ እየታየኝ ነው” መጡ… መጡ…
፡ሕዝብ፦ “አሜን”
ሁለት በሱፍ የተወጠሩ ጎረምሶች ወደ መድረክ ወጡ።
:ካራቲስቱ፦ ሻምፓራራራራራራራራም…ራም…ራም አለና ሁለቱን ጎረምሶች በጠረባ ጣላቸው። ሕዝቡ በጩኸትና በፉጨት አዳራሹን አቀለጠው። ጎረምሶቹ መሬት ላይ ተዘርረው ወደቁ። ሻራም…ራም…ሪራቶማራም…ሾራም… ቲራ ታራምም… አለ። ልሳን መሆኑ ነው። ድንቄም ልሳን! ቀጠለና ካራቲስቱ የተዘረሩትን ጎረምሶች ጀርባ ጀርባቸውን በካልቾ ይለጠልጣቸዋል። ሕዝቡ ጩኸቱንና ፉጨቱን ሪታውን ጭምር ያቀልጠዋል። “ተነስ” ራም ቱራም ራም ሾም ታራም…… አለ። ጎረምሶቹ ከተዘረሩበት ተፈነጣጥረው ተነሱ። ሕዝቡ እሪ እያለ አዳራሹን በጠበጠው። ከጫፍ ጫፍ ሪታውንና ፉጨቱን ያቀልጠዋል። ጩፋ ሙት አስነሳ ማለት ነው።

እኔ የጩፋ ቀልድና ማላገጥ አይደለም የገረመኝ። ሕዝቡ ይህን ቀልድ መቀበሉ ነው። ሕዝቡ ግን አይምሮውን ማን ሰረቀው? በዚህ ዘመን ሴቶቻችን የሚጠቀሙት አርቲፊሻል ፀጉር አለ። “Human Hair” ይሉታል። የዚህ ሕዝብ አይምሮም አርቲፊሻል ሆነ እንዴ? “Human Hair” እንዳሉት “Human made” Mind ተገጥሞላቸው ይሆን? የእውነት “ጩፋ ማይንድ” ናቸው። እንዲህ አይነት አንጃ ልፍለፋዎች የሚተላለፉባቸው የፕሮቴስታንቱ የቢዝነስ ቲቪ ጣቢያዎች ብዙ ናቸው። ይህን ቅርሻት ሲጋት የሚውል ሕዝብ አርቴፊሻል አይምሮ የተገጠመለት ነው። ፈዝዞ ደንዝዟል!

ይህ እንግዲህ ሃገርህን፣ ሰውነትህን፣ ሃይማኖትህን እንድትዘነጋና ነፈዝና ጅል ሆነህ እንድትቀር የተዘረጋልህ መረብ ነው።

ከዚህ ባሻገር ምዕራባዊያን ሌላ የአፍዝዝ አደንዝዝ ሥርዓታቸውን የሚግቱህ ዘመናዊ ትምህርት ቤት ተብሎ በተገነባልህ ትምህርት ቤትና ዩኒቨርስቲህ ነው። የትምህርት ተቋማቶቻችን አንድም ለትውልድ የሚጠቅም አድርገው አይሠሩህም። ባዶ ቅሪላ ነው የሚያደርጉህ። ተቋማቱ ስለሃገርህ ጀግኖች አይነግሩህም። ስለኢትዮጵያ ታላቅነት አያስተምሩህም። እነሱ አሁን ላሉበት “ስልጣኔ” (እንበለው) የበቁት ካንተ በዘረፉት ጥበብ እንደሆነ አይነግሩህም። ይልቁንም ዘረኛ እንድትሆንና ራስክን ባዶ እነሱን ትልቅ አድርገህ እንድታውቅ ያስገድዱሃል። የእነሱን ርባን የሌላቸው ቲዎሪዎችና ገልቱ አፍዛዥ ወሬዎች ይግቱሃል። የመጀመሪያዎቹ ስነፈለክን ያጡነት ኢትዮጵያዊያኑ ነገሥታት”ካሲዮጵና አንድሮሜዳ” እንደሆኑ ይደብቁሃል። የመጀመሪያው ጀነቲክ ኢንጅኔዬር ኢትዮጵያዊው “ንጉሥ ኢትኤል” እንደሆነ አይነግሩህም። ለዓለም ዕውቀት ምንጮች ኢትዮጵያዊያን እንደሆኑ እንድታውቅ አይፈልጉም። ጭራሽ ለዓለም ብርሃን የሆኑ ሊቃውንት መፍሉቂያ የሆኑትን “የአብነት ትምህርት ቤቶችን” ንቀህና አንቋሸህ የእነሱን ተረት የምትነዛ ፈዛዛና ከንቱ ያደርጉሃል።

ይህንና ሌላውን በዚህ አጭር ፅሑፍ መግለፅ የማልችለውን ሕቡዕ ጥበብ የሚናገሩ አንዳንድ ሊቃውንትና የኢትዮጵያዊነት ልህቀት የሚያንገበግባቸው ሰዎች ብቅ ሲሉ “የድሮ ሥርዓት ናፋቂ፤ አፄ፣ ወዘተ…” እያሉ የሚያሸማቅቂ ቅጥረኞችን ከጎንህ አስቀምጦ ዝም እንድትል ያደርግሃል። “ያልገባው፤ ፋራ፣ …” እያሉ ዝም የሚያደርጉህን ባዶ ወሬኞችን አጠገብህ ያስቀምጥብሃል።

እውነትን መናገርና ለእውነት መኖር የሚያሳስርበትን፣ የሚያስገርፍበትን፣ የሚያስገድልበትን… ሥርዓት ይሾምብሃል። እኛ ግን ሃገራችን ኢትዮጵያ፣ ሃይማኖታችን ተዋሕዶ ነው። ይህንንም ማንም ሰው አልሰጠንም። ልዑለ ባሕሪ እግዚአብሔር ለማንም ለሌላ ያልሰጠው ለእኛ ብቻ የሠጠን ነው። ይህንን እውነት ደግሞ ማንም ኢትዮጵያዊ ሊያውቀውና ሊናገር የተገባ ነው። በቃ… ዝምታው ይብቃ! ኢትዮጵያዊነት ከፍ ይበል። የማንንም እንቶ ፈንቶ መስማት ይቅር!

ከዚህ ጋር በተያያዘ “ዝም በል” የሚሰኝ ግሩም ግጥም በዲያቆን መኩሪያ ጉግሣ ቀርቦልናል። በእውነት ዝም አንበል! ይህን ግጥም አዳምጡት። የድምፅ ግጥሙንም እንደሚከተለው አስፍሬዋለሁ፤ ማዳመጥ ያልቻለ ያንብበው።

ዝም በል

አገርና ሃይማኖት ይለያል ይሉኛል፣
ኢትዮጵያን ክብሬን ስል…
ይሄን ፖለቲካ አስቀምጠው ይሉኛል፣
አፌን ያስይዙኛል፣
መንግሥትን መገሰፅ አትችልም ይሉኛል፣
ምዕራፍ ቁጥር ጠቅሰው ሙግት ይገጥሙኛል፣
ይከራከሩኛል።

የእግዚአብሔር መንግሥት በሚሰበክበት፣
ሥጋውና ደሙ በሚፈተትበት፣
ይሄን የማርክስን የፑሉቶን እብደት፣
የእነ ፍሮይድ’ን፣ የእነ አፍላጦንን ፍልስፍና ቅዠት፣
የእነ ሂትለርና የእነ ሞሶሎኒ የጭካኔ ዝቅጠት፣
አትችልም በአትሮንሷ ልትዘባርቅበት፣
እያሉ ይሉኛል፣
አፌን ያስይዙኛል፣
ትርጉሙን አፋልሰው ግራ ያጋቡኛል።

ሲገድሉህም ዝምበል ሃይማኖተኛ ነህ፣
ሲዘርፉህ ተዘረፍ መንፈሳዊ ሰው ነህ፣
ፍርድ ቢጓደልም ደሃዋ ብታለቅስ፣
ራሷ ትወጣው አታምጣው ከመቅደስ፣
አንተ ምን ቸገረህ? ሥራህ እንደው መቀደስ!፣
የተገደለች ቀን ለፍትሐቷ መድረስ።
እያሉ ይሉኛል፣
ሕይወቷን ነጥቀውኝ ሞቷን ይሠጡኛል።

ድንገት ትክ ብዬ…
በእጄ ላያ ያለውን አርዌ በትሬን ሳየው፣
ሙሴ ሲዋቀሰኝ ሲሟገተኝ አየሁ፣
ዝምታህን ስበር ወይ በት’ሬን ተወው።
እያለ ወቀሰኝ፣
ቃሉን አስታወሰኝ።

ለሕዝቡ ነፃነት ከፈርዖን ቤት ወጥቶ፣
የግብፅን ብዙ ወርቅ ምቾቱን ሰውቶ፣
አብሯቸው ሲሰደድ ብድራቱን አይቶ፣
ትዝ አለኝ ታሪኩ፣ ትዝ አለኝ ጭካኔው፤
ሕዝቡ አምላክ በድሎ ላጠፋው ነው ሲለው፤
ከሕይወት መፅሐፍ ደምስሰኝ እንዳለው፤
ይሄንን ዘፀአት አምጥቶ ፊቴ ላይ ድንገት ዘረገፈው።

ነገረኝ አጥብቆ… ሕዝብ አገር ሳይኖረው፣
እምነት ብሎ ነገር፣
ኪዳን ብሎ ነገር፣
ባሕልና ትውፊት እንደማይሞከር።

ለዚህ ነው ፈርዖንን “ሕዝቤን ልቀቅ” ያለው፣
ግብፅ ምድር ሳለ ኪዳኑን ያልሠጠው፣
ታቦቱን ያልሠጠው፤
የፂዮን ዝማሬ በባቢሎን ወንዞች እንዳይዘመር ነው።
ታዲያ ለምንድነው?
እኔስ ፈርዖኖቼን፣
እኔም ጨቋኞቼን፣
ተው! እንዳልላቸው፣
ዝም በል የምባለው?
በሃይማኖት ሰበብ፣
አገሬን ሲነጥቁት ቁጭ ብዬ የማየው፣
መስዋዕቴን ወስጄ የት እንድሰዋው ነው?

ኧረ ዝም አልልም፤ ማንስ ዝም እንዳለው?!
ርስቱን ተነጥቆ ናቡቴ ሲገደል፣
ኤልያስ ዝም አለ?!
ንጉሡን ገስፆ እጥፍ ያስከፈለ፣
ታዲያ ምን አገባው? ሃይማኖት አይደለ!
አንድ ደሃን እንጂ አክዓብ ያስገደለ።

ኦዝያን ንጉሡ ወደ መቅደስ ገብቶ፣
የአሮንን ክህነት በሥልጣን ቀምቶ፣
ለማጠን ሲጀምር በድፍረት ተሞልቶ፣
ካህኑ አዛርያስ መች ዝም አለው ከቶ?!
መቅደሱን እስኪለቅ ጨርሶ እስኪወጣ፣
ቦታ አልነበረውም ለንጉሡ ሥልጣን ለኦዝያን ቁጣ።

ኢሳያስ ነው እንጂ፣ ኢሳያስ ነቢዩ፤
ይሄን ድፍረት አይቶ፣
በዝምታ ቢያልፈው ንግሥናውን ፈርቶ፣
እግዚአብሔር ተቆጣ ትንቢቱን ነጠቀው፣
ከናፍሩን መታ በለምፅ አነደደው፣
በዝምታው ሰበብ እግዚአብሔር ተለየው።

ይሄን እያያችሁ አፌን አትለጉሙኝ፣
ዝምታ እመም እንጂ፤ “ወርቅ ነው” አትበሉኝ፣
ባለቦታው ተረት ልቤን አታድክሙኝ፣
ላገሬ ለእምነቴ ልጩህላት ተውኝ።

ያ! ጃንደረባ’ኮ ፊሊጶስ ያገኘው፣
ብሉይ ኪዳን ይዞ መንፈስ ቅዱስ ያየው፣
በማመን ሲጠመቅ በሐዲሱ ኪዳን፣
በልቡ መቅደስ ውስጥ ይዟት ነው ኢትዮጵያን።
መጥቶ የነገረን ይህንን ምስጢር ነው፣
እኛም በክብር ይዘን ጠብቀን ያኖርነው፣
ጠዋትና ማታ በዜማ ምንጮኸው።

ተዋሕዶ እምነቴ፣
ኦርቶዶክስነቴ፣
ያገሬ ፀጋ ነው፤
ኢትዮጵያዊ ባልሆን ከሌላ ምድር ላይ የማልቀበለው።
ታዲያ ሃይማኖቴን፣
ከኢትዮጵያዊነቴ፣ እንዴት ነው ምለየው?

እምዬ ምኒሊክ በድንግል ስም ምለው…
አዋጁን ያወጁት፣
የግምባሯን ማሪያም፤
ያራዳውን ጊዮርጊስ ይዘው የዘመቱት፣
ባንድነት ቢያምኑ ነው፣
አገሩን ከእምነቱ ለይተው ባያዩት።

አቡኑም ይናገር ጴጥሮስ ሰማዕቱ፣
እንኳን ሰውን ቀርቶ ምድርን መገዘቱ፣
ባንድነት ሲቆም ነው ላገሩ ለእምነቱ።

እናም ይበቃኛል ዝም በል አትበሉኝ፣
ብትሉም… አልልም!፤
ከሚሞት ጋር እንጂ ገዳይ ጋር አልቆምም።
ሕዝብ ሳይኖር አገር፣
አገር ሳይኖር እምነት በፍፁም አይኖርም።

የኢትዮጵያን ትንሣኤ ቅርብ ነው!

Share.

About Author

Comments are closed.